በዴልፊ ኤአይ (Delphi AI) አማካኝነት የሰውን ልጅ አእምሮ በዲጂታል መንገድ መቅዳት (Clone) የሚያስችል አዲስ የቴክኖሎጂ ምዕራፍ ተጀምሯል።
የዚህ ኩባንያ መስራች የሆነው Dara Lajevardian
እንደሚለው፣ አዲሱ ቴክኖሎጂ አንድ ሰው በህይወት ዘመኑ ያካበተውን እውቀት፣ አመለካከትና የአነጋገር ዘይቤ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ወደ ዲጂታል አምሮት መቀየር ይችላል። ይህ የቴክኖሎጂ ውጤት ተራ የውይይት መተግበሪያ ሳይሆን፣ ግለሰቦች ያሏቸውን መረጃዎች ማለትም ፖድካስቶችን፣ የማህበራዊ ሚዲያ ጽሁፎችንና መጽሐፍትን በመጠቀም የእነሱን ማንነት የሚወክልና ከሰዎች ጋር በድምጽም ሆነ በምስል መገናኘት የሚችል ዲጂታል ወኪል የሚፈጥር ነው።
የዚህ አስገራሚ ፈጠራ መነሻ የሆነው የ Dara Lajevardian የግል የህይወት ታሪክ ነው። የ Dara Lajevardian አያት በኢራን ውስጥ ስኬታማ ነጋዴ የነበሩ ቢሆንም፣ በደረሰባቸው የስትሮክ አደጋ ምክንያት የመናገር ችሎታቸውን አጥተው ነበር። Dara Lajevardian ከአያቱ ጋር የነበረውን ጥልቅ ግንኙነትና የእውቀት ሽግግር ለማስቀጠል ባለው ፍላጎት፣ በአያቱ የተጻፉ መዝገቦችንና ታሪኮችን ወደ ኤአይ ሞዴል በመቀየር ለመጀመሪያ ጊዜ የአያቱን ዲጂታል ቅጅ ፈጠረ።
ይህ ስኬትም Ray Kurzweil
“How to Create a Mind” በሚለው መጽሐፋቸው ከገለጹት የሰው ልጅን አእምሮ በሶፍትዌር የመገንባት እሳቤ ጋር ተዳምሮ ለዴልፊ ኩባንያ መመስረት ምክንያት ሆኗል።
በአሁኑ ወቅት እንደ Jay Shetty,
Eckhart Tolle
እና Arnold Schwarzenegger
ያሉ ታዋቂ ግለሰቦች የራሳቸውን ዲጂታል ክሎን በመጠቀም በዓለም ዙሪያ ካሉ አድናቂዎቻቸው ጋር 24 ሰዓት በተግባቦት ላይ እንዲቆዩ አስችሏቸዋል።
ቴክኖሎጂው ተጠቃሚዎች መረጃዎቻቸውን እንዲጭኑና በ15 ደቂቃ ውስጥ የራሳቸውን ዲጂታል ቅጅ እንዲያገኙ የሚያደርግ ሲሆን፣ ይህም ወደፊት መጽሐፍትን ከማንበብ አልፎ ከደራሲው ዲጂታል ማንነት ጋር በቀጥታ በመወያየት እውቀት ለመቅሰም ያስችላል።
ይህ የኢንተርኔት የወደፊት ጉዞ ተደርጎ የተወሰደው ፈጠራ፣ የሰውን ልጅ እውቀትና ትውስታ ለዘለዓለም በዲጂታል ዓለም ውስጥ ለማቆየት ትልቅ ተስፋን ይዞ ብቅ ብሏል።
የDara Lajevardian ታሪክ በቀጣዩ ቪዲዮ ይመልከቱ።





Leave a Reply